የክልል ልዩ ኃይሎች በኢትዮጵያ፡- የአደረጃጀት፣ ሚና፣ ሕገመንግስታዊነት እንዲሁም መፍረስ

አንዱአለም ነጋ ፈረደ (ረዳት ፕሮፌሰር በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ)

7/25/2023

An Afar Special Force Soldier, Bisober (AFP, 2020)
An Afar Special Force Soldier, Bisober (AFP, 2020)

መንደርደሪያ

የኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ በአጼ ምኒሊክ 2 ዘመነ መንግስት ጀምሮ ከተማ ዘበኛበሚል ስያሜ የተጀመረ ሲሆን፤ በተደራጀ እና በዘመናዊ መልኩ ብሪቲሽ ፖሊስቅርጽን ይዞ የተጀመረዉ ግን 1934 .. በታወጀዉ የንጉስ አዋጅ ቁጥር 6/1934 መሰረት ነዉ።አመራሩም በብሪቲሽ ዜጎች ስር ነበር፡፡1 1974 .. ከንጉሱ ስርዓት ማብቃት በኋላ ደርግ በአዋጅ ቁጥር 10/1974 የሀገሪቱን ጸጥታ የሚያስጠብቅ አዲስ የፖሊስ ስርዓት አዉጇል፡፡ ኢህአዴግ በአዋጅ ቁጥር 1/1995 ረጅም ዘመን ያስቆረዉን የፖሊስ አደረጃጀት በሚቀይር መልኩ ከተማከለ አደረጃጀት ወደ አልተማከለ አደረጃጀት ቀይሮታል፡፡ በይዘቱም የሁለትዮሽ (dual structure) እዉን አድርጔል፡፡ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 51(6) የፌደራል መንግስቱን ስልጣንና ተግባር ያትታል፡፡ በዚህም የፌደራል መንግስቱ ብሄራዊ የመከላከያ ሃይልን እና የፌደራል ፖሊስ ሃይል እንደሚመሰርት እና እንደሚያስተዳድር ይገልጻል፡፡2 በተመሳሳይ በአንቀጽ 52(2)() የክልል መንግስታት የየራሳቸዉን ፖሊስ እንደሚመስርቱ እና እንደሚያስተዳድሩ የክልላቸዉን ሰላም እና ደህንነት እንደሚያስጠብቁ ይገልጻል፡፡ ይህንን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ ተከትሎ 1 የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ 11 የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች፤ 2 የከተማ አስተዳድር ፖሊስ ኮሚሽኖች እና በዉስጣቸዉ ለመቁጠር የሚያዳግቱ ልዩ ልዩ አደረጃጀት ያላቸዉ የፖሊስ መዋቅሮች ተፈጥረዋል፡፡

ከነዚህ አደረጃጀቶች አንዱ የልዩ ሃይል አደረጃጀት ነዉ፡፡ ልዩ ሃይል አመሰራርቱ ኦብነግ 70 በላይ በቻይና ነዳጅ ፈላጊ ባለሙያዎች እና ኢትዮጵያዊ ዜጎች በሚያዚያ 2007 .. አቦሌ ላይ የፈጸመዉን ጥቃት እና በግንቦት 2007 .. በሶማሌ ክልል ፕረዝደንት አብዱላሂ ሀሰን ላይ በጅጋጅጋ ከተማ ያደረሰዉን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ ነዉ፡፡3 እነዚህ ክስተቶች በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ሞቃዲሾ ዉስጥ ከሶማሊ ሸማቂ ሃይሎች ጋር ጦርነት በሚያደርግበት ወቅት መከወኑ ለዉልደቱ ቅጽበታዊ ምክንያቶች /Imidiate Couses/ ነበሩ፡፡4 ለሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል መፈጠር ዋናዉ ቁልፍ ምክንያት/Root Couse/ ተደርጎ የሚወሰደዉ፣ በወቅቱ የነበረዉ መንግስት ኦብነግን ለመዋጋት ተመሳሳይ አደረጃጀት ያለዉ ሃይል አስፈላጊ ነዉ ብሎ በማመኑ ነበር፡፡5 ይህ ሃይል በአንዳንዶች አገላለጽብሶት የወለደዉእና ለማህበሰቡ እንደመሲህየሚቆጠር ነበር፡፡6 የሚመለመሉትም ከተመሳሳይ ጎሳ እንደነበር ይወሳል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሃይሎች የአካባቢዉን መልክዓ ምድር እና የማህበረሰብ ትስስር ጠንቅቀዉ የሚያዉቁ እና አከባቢዉን ለመቃኘት እና ሰርጎ ለመግባት ቁልፍ ሚና ነበራቸዉ፡፡7 ለዚህም ኦብነግን የከዱ እና በእስር ላይ የነበሩ የኦብነግ አባላት ሳይቀሩ ይመለመሉ እንደነበር ይወሳል፡፡8 በሂደትም ልዩ ሃይሉ ለሶማሌ ክልል ሁነኛ የጸጥታ ሃይል እና በሀገር አቀፍ እና አለምዓቀፍ ስምሪቶች ሳይቀር የሚሳተፍ ሀይል ሆኖ ብቅ አለ፡፡ ይህንን የሶማሌ ክልል ተሞክሮ ያዩ የክልል መንግስታት ላለፉት 15 ዓመታት የተደራጁ ልዩ ሃይሎችን መፍጠር እና የየክልላቸዉ አዳኝ/Savior/ አድረገዉ መመልከት መሬት ላይ ያለ ሀቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ይህ የልዩ ሃይል አደረጃጀት ከተመሰረተበት ጀምሮ የህገ-መንግሰታዊነት፣ የአደረጃጀት፣ የሃላፊነት፣ የምልመላ፣ የትጥቅ ተገቢነትና ሌሎቸም ጥያቄዎች ይነሱበት ነበር፡፡ ከቅርብ ግዚያት ወዲህ ይህ ሀይል ያለው አደረጃጀት እና ሚና ለሀገራዊ ዘላቂ ሰላም፣ ለጋራ ደህንነት እና መፃኢ ተስፋ ሲባል መፍረስ እና ወደ መደበኛ ፌደራል እና ክልል ፖሊስ ስርዓት ውስጥ መካተት አለብት የሚል አቅጣጫ፣ ምልከታ እና አፈፃፀም ጠንክሮ ይታያል። ይህ ፅሁፍ ይህንን እሳቤ በመቃኘት ልዩ ኃይሉ ላይ እሚነሱትን የአደረጃጀት፣ ሚና፣ ሕገመንግስታዊ ጥያቄ እንዲሁም በማፍረስ ሂድት ውስጥ ያለውን ምልከታ በአንክሮት ይቃኛል።

ልዩ ሃይሎች ሚና እና አደረጃጀት

የክልል ልዩ ሃይላት በስርዓቱ የሰለጠኑ እና ሽምቅ ዉጊያ ለማድረግ የሚያስችል ትጥቅ የታጠቁ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳ ልዩ ሃይል ሲመሰረት ሽምቀን ለመዋጋት እና አድማ ብተናን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም በሂደት የልዩ ሃይሎች ሚና ተቀይሯል፡፡9 የክልላቸዉን ሰላም ከመጠበቅ በዘለለ፣ ለሚፈጠሩት ድንበር ዘልል የጸጥታ ስጋቶች፣ በፌደራል መንግሰቱ እና በክልሎች መካከል እየተፈጠሩ ለነበሩ አለመተማመኖች፣ እንዲሁም በክልሎች መካከል ለነበሩ ግጭቶች እንደምክንያት ይጠቀሱ ነበር::10 ልዩ ሃይሎች በነበራቸዉ ሚና እና በያዙት የረቀቀ ትጥቅ፣ የሃይል ብዛት፣ የተመልማይ መሰረት፣ የስልጠና ጥራት፣ እና ከመንግስት በተቃራኒ ከቆሙ ሀይሎች ጋር ካላቸዉ የስነ- ልቦና ትስስር ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱ የአንድነት ስጋት እየሆኑ መጥተዉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዉስታ ነዉ፡፡

ልዩ ሃይሎች በአደረጃጀት፣ በምልመላ፣ በቅጥር፣ በስልጠና፣ በሚታጠቋቸዉ መሳሪያዎች፣ በስምሪታቸዉ እና በአጠቃላይ አላማቸዉ ከተመሰረቱበት ጊዜ አንጻር በእጅጉ ተይተዉ ነበር፡፡11 ከመጠን አንጻር በዋናነት ሶሰቱ ክልሎች ማለትም ኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ቁጥራቸዉ በዉል የማይታወቅ በተለያዩ ዙሮች እጅግ ብዙ ልዩ ሃይሎችን ሲያስመርቁ ይስተዋሉ ነበር፡፡ ሌሎችም ክልሎች የእነዚህ ሶስት ክልሎችን ተመክሮ በመከተል ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ላይ ነበሩ፡፡

አደረጃጀታቸዉም ልክ እንደመከላከያ ሃይል በእዞች፣ ባታሊዮኖች እና ምድብተኞች የተደራጁ ነበሩ፡፡ ትቃቸዉ ከመከላከያ በብዙ የሚለይ አልነበረም፡፡ ዘመናዊ የእጅ መሳሪያዎቸ፣ M40 ሪፍል፣ ስናይፐር፣ ዲሽቃ፣ እና ከመከላከያ የተወሰዱ ከባድ መሳሪያዎችን ጨምሮ የታጠቁ ነበሩ፡፡12 ልዩ ሃይሎች ይወስዱት የነበረዉ ስልጠና በይዘቱ የፖሊስ ሳይሆን የመከላከያ ነበር፡፡ ቦታዉም ከመደበኛ ፖሊስ የሚለይ እና ለተግባር ልምምድ በሚያመች መልኩ የተመረጠ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ የመከላከያ ማሰልጠኛ ቦታዎችን ይጠቀሙ ነበር፡፡ የመደበኛ ፖሊሶች ስልጠና ህጎች እና ፖሊሲዎች ላይ ሲያተኩሩ፤ ልዩ ሃይሎች ግን ትኩረት የሚያደርጉት የአካል ብቃት፣ ስልታዊ መከላከል፣ ጸረ ሽምቅ እና ማጥቃት ላይ ነበር፡፡ 90% የተግባር ልምምድ እና የኮማንዶ ክህሎትን ያካተተ እንዲሆን ይደረግም ነበር፡፡13

ልዩ ኃይሎች ላይ የሚነሳው የህገ መንግስታዊነት ጥያቄ

የህገ መንግስታዊነትን በተመለከተ አሁን ያለዉን ማንነትን መሰረትን ያደረገ ስርዓትን የሚቃወሙ (Centrists) ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ወይም ያልተማከለ አህዳዊ ስርዓት እዉን እንዲሆን ከማሰብ አንጻር መከላከያ እና ፌደራል ፖሊስ የበለጠ እንዲጠናከሩ ከማሰብ አንጻር የልዩ ሃይል አደረጃጀትን ከአላማዉ በመነሳት -ህገ መንግስታዊ ያደርጉታል፡፡ አደረጃጀቱ ቸል ከተባለ የብሄር ብሄርተኝነትን ስለሚያበረታታ በሂደት ወደ ሁሉን አካታች ጦርነት፣ መከፋፈል እና የብሄር ግጭት ሊያመራ ይችላል ብለዉ ያምናሉ፡፡ በእነዚህ አካላት አረዳድ፣ በህገ- መንግስቱ የክልል መንግስታት ፖሊስን ያደራጃሉ ሲል የመከላከያን ሚና የሚተካ ኃይል ያደራጃሉ ማለት አንዳልሆነ ይሞግታሉ፡፡ ህገ መንግስቱ በዋናነት ታሳቢ ያደረገዉ በክልላቸዉ ዉስጥ ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ የሚያስችል የመደበኛ ፖሊስ ህግ የማስከበር ስራዎችን የሚያስቀጥል እነጂ የተደራጀ፣ የሰለጠነና የመከላከያ ተፈጥሮ ያለዉ አይደለም ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ ይህንን የህገ መንግስቱን ይዘት ለመረዳት በህገ መንግስት ማርቀቅ ሂደት ዉስጥ የነበዉንሀተታ ዘምክንያትማየት ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ አንቀጽ 52(2)() ላይ በነበረዉ ዉይይት፣ የፖሊስ ሚና የህዝብ አገልግሎት መስጠት እና የህዝብን ጸጥታ ማስጠበቅ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ የየክሎቹ ህገ መንግስት ሲፈተሽም፣ አንዳቸዉም ስለ ልዩ ፖሊስ የጠቀሱበት ቦታ የለም፡፡ ይህም የህግ መሰረት የሌለዉ እና በህገ መንግሰት ድጋፍ የሌለዉ ነዉ ሲሉ ያጠቃልላሉ፡፡14

በሌላ በኩል አሁን ያለዉን ማንነትን መሰረት ያደረገ ስርዓት የሚደግፉ ሃይሎች (Ethno-Nationalists) እንደ ኢትዮጵያ ማንነቶች በበዙበት ሀገር፣ በፖለቲካ ኢሊቱ ላይ አነስተኛ እምነት በመኖሩ እና ህዳጣን ተሰባስበዉ የመሰረቱት ሀገረ መንግስት ስለሆነ፣ እራስን ማስተደደር ብቸኛዉ ብዙ ሁኖ የመታየት ልምምድ ነዉ ይላሉ፡፡ የክልሎች እራሳቸዉን ከማዕከል ተቋማት ተጽዕኖ የመከላከል መብት ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ በመሆኑም ልዩ ሃይል የራስን ማስተዳደር አካል ተደርጎ የሚወሰድ እና ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 8, 39, 46, and 47 የሚቀዳ እንደሆነ ያወሳሉ፡፡ እነዚህ የህገ መንግስት አንቀጾች ከአንቀጽ 52(2) () መንፈስ ጋር በእጅጉ የሚገናኙ እንደሆነም ያወሳሉ፡፡ የክልል የፖሊስ የማደራጀት ስልጣንን የመገደብ ፍላጎት ቢኖር ኖሮ አደረጃጀት፣ ትጥቅ፣ ሚናዉን ሊወስን የሚችል የጋራ ሃይል ወይም ህግ ያስቀምጥ ነበር ብለዉ ይሞግታሉ፡፡

በልሂቃን ይሰነዘሩ የነበሩ የመፍትሄ አቅጣጫዎች

የፖሊስ አደረጃጀትን በተመለከተ አሁን ያለዉ የሁለትዮሽ/dual/ ፌደራሊዝም በኢሊቶች መካከል በቂ መግባባት ባልተፈጠረበት እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የጸጥታ ጉዳዮችን የሚያሳልጡ ጠንካራ ተቋማት ባልተገነቡበት ሁኔታ እንደ ሲዉዘርላንድ እና አሜሪካ ፌደሬሽኖች፣ የፖሊስ ስልጣንን ለክልሎች ለጥጦ መስጠት፤ ልዩ ሃይሎች ደቅነዉ የነበሩት ዓይነት አደጋ መከሰቱ አይቀሬ ነበር፡፡ በመሆኑም የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅን ጨምሮ የዘርፉ ልሂቃን ሁለት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ይሰነዝሩ ነበር፡፡

እንደ የአጭር ጊዜ መፍትሄ፡- ይህ መፍትሄ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ የማያስፈልገዉ ነገር ግን የፌደራል መንግስቱ እና የክልል መንግስታትን ቅን ልቦና/goodfaith/ የሚጠይቅ ነዉ፡፡ ይህም ህገ መንግስቱ ክልሎች የፖሊስ ሃይል እንዲያቋቋሙ ሲደነግግ፣ የዉስጣቸዉን ሰላምና ደህንነት እንዲያስጠብቁና ራስን የማስተዳር ስልጣን መገለጫ በመሆኑ እንጂ መከላከያን የመተካት ስራን እንዲሰሩ እንዳልሆነ በቅን ልቦና መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ይህም በህገ መንግስት ማርቀቅ ሂደት ቃለ ጉባኤ /ሀተታ ዘምክንያት/ በአግባቡ መመላከቱን ማጤን እና መረዳት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ በዚህ መንፈስ የልዩ ሃይል ሚና እና አደረጃጀት ወደ መደበኛ ፖሊስ ኃይል ሚና እና አደረጃጀት መመለስ እና የትጥቅ፤ የምልመላ፣ የስልጠና ሁኔታን ማስተካከል ግድ ይል ነበር፡፡15 በመሆኑም በጊዚያዊነት ልዩ ሃይል ትጥቅ ፈትቶ እና ከእንቅስቃሴዉ ተገትቶ በሀገሪቱ ህጎች እና አለምኣቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ተገዢ በሆነ መደበኛ የክልል የፖሊስ ሃይል አንዲኖር እና ይህ ኃይል በዚህ የጋራ መድረክ እንዲመራ ማድረግ ተገቢ ነበር፡፡ በመሆኑም በሁለቱ ስምምነት እንደ ተቋም ከመከላከያ ይዘት የተለዬ፣ ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ፣ ዲሞከራሲያዊ እና አገልግሎቱ ተደራሽ (ያልተማከለ) የፖሊስ ሃይል ማደራጀት ይጠይቃል፡፡16

ዘላቂ መፍትሄ፡-ይህ የመፍተሄ ሃሳብ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግን የሚጠይቅ ነዉ፡፡እንደ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የተማከለ የፖሊስ ስረዓት መፍጠር ሳያስፈልግ የተገደበ ስልጣን ያለዉ የክልል ፖሊስ ማደራጀት እና ከፍተኛ የጸጥታ ችግሮችን በፌደራል ፖሊስ ወይም በመከላከያ እንዲሸፈን ማድረግን ያካትታል፡፡ ይህ ገደብ በህገ መንግስቱ መመላከት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን የክልሎች ራስን የማስተዳደር መብት ችግር ላይ የማይወድቅበት አማራጭ መፈለግን ያካትታል፡፡ ሌላዉ በዚህ ስር የሚካተተዉ እና ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልገዉ በዋናነት በጀርመን፣ በመጠኑ በህንድ የሚተገበረዉ መርህ ሲሆን የፌደራል መንግስቱ ጠቅላይ ህጎችን /Framework Legislation/ እንዲያወጣ ማድረግ እና ህጎችን ማስፈጸም እና ማስረዳደር የክልሎቹ እንዲሆን ማድረግ ነዉ፡፡ በዚህም ህግ ስልጠናችዉን፣ ሀላፊነታቸዉን፣ የስምሪት ደረጃን፣ የሚይዙትን መሳሪያ መወሰን ይቻላል፡፡

በጥቅሉ በፌደራል እና በክልል መንግስታት መካከል ግልጽ ስልጣን ክፍፍል ማድረግ የግድ ይላል፡፡ የሁለቱ ፖሊስ ስልጣንም በአግባቡ መሰመር አለበት፡፡ የክልል ፖሊሶች ከክልላቸዉ የዉስጥ ጸጥታ ላይ ብቻ እንዲገደቡ ማድረግና ከክልላቸዉ ዉጭ እና በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንዳይኖራቸዉ ማድረግ ለፌደሬሽኑ ጤናማነት በእጅጉ አስፈላጊ ነዉ፡፡

መንግስት ልዩ ሃይልን ያፈረሰበት ሂደት

መንግስት የተከተለዉ የመጀመሪያዉን የመፍትሄ አቅጣጫ ነዉ፡፡ በመርህ ደረጃ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ የመንግሰትን ዉሳኔ አይቃወምም፡፡ ዉሳኔዉ የተተገበረበት ሂደት (procedure) እና ይሰጡ የነበሩ አመክንዮች ላይ ግን ሰፊ ችግሮች እንደነበሩ ያምናል፡፡ በመጀመሪያ ይህ ሃይል የተደራጀዉ አስፈላጊዉ ግባት ተሟልቶለት በየክልል ምክር ቤቶች ይሁንታ እና ፈቃድ ሆኖ እያለ በማፍረስ ሂደት ዉስጥ እነዚህ አካላት በግልጽ አለመሳተፋቸዉ እና የፈጠሩትን አካል በማፍረስ ሂደቱ አለመሳተፋቸዉ እነዚህን አካላት ቅር ከማሰኘቱም በላይ የህጋዊነት እና የቅቡልነት ጥያቄ እንዲነሳበት አድርጔል፡፡ የፌደራል መንግስትና የክልሎች የትብብር እና የመከባበር የፌደራል ስርዓት ግንባታንም ጥያቄ ዉስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ይህም ሌላ የኢ-ህገመንግስታዊነት አመክንዮን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ይህ ባለመደረጉም ዉሳኔዉ የተለያዬ ትርጉም ተሰጥቶት የልዩ ሃይል መፍረስን፤ የሀገሪቱ ችግር የመፍትሄ አካል አደርነገዉ ይወስዱ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሳይቀር አንዲጠራጠሩት እና እንዲቃወሙት አስገድዷል፡፡ በማስፈጸም ሂደትም ከፍተኛ ችግር ገጥሞት ቆይቷል፡፡ ሌላዉ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳዉ የጉዳዩ ድንገቴነት ነዉ፡፡ ይህ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያን ሳይቀር (በተወሰኑ ልሂቃን የሚደገፍ ነዉ) ግድ የሚለዉ ጉዳይ ሆኖ እያለ እና የጉዳዩ ባለቤቶችን (ልዩ ሃይሎችን) ማወያየት፤ ማስረዳት እና ማሳመን የሚጠይቅ ተግባር ሆኖ ጉዳዩ በፖለቲካ ዉሳኔ ማለቁ በራሱ የራሱ የሂደት ችግሮች እንደነበሩበት ያሳያል፡፡

ከአመክንዮ ጋር ተያይዞ የሚነሳዉ እና ጉዳዩን እንዲያስፈጽሙ ስልጣን የተሰጣቸዉ አካላት ለመፍረሱ ደጋግመዉ የሚጠቅሱት የልዩ ሃይልን አደረጃጀት -ህገ መንግስታዊነት በመጥቀስ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ የዘርፉን ልሂቃን ለሁለት አቧድኖ በሚያከራክርበት እና መቋጫ ባልተገኘበት ሁኔታ ለመፍረሱ እንደ አመክንዮ መጠቀሱ የአንድ ወገን እይታን እንደመደገፍ ይቆጠራል፡፡ ይልቁንም በዚህ የህገ-መንገስታዊነት ጥያቄ ላይ የመጨረሻ ብያኔ ለመስጠት የሁለቱ ወካይ አካላት ጥልቅ ዉይይት እና ቅቡልነት የሚፈልግ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ ሳይሆን በመቅረቱ የመፍተሄ እርምጃዉ በእነዚህ ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ አድረጎታል፡፡

በአጠቃላይ የልዩ ሃይል ለዘላቂ ሰላም፣ ለጋራ ደህንነት እና መፃኢ ተስፋ የመፍረሱ ዉሳኔ አጠያያቂ ባይሆንም፤ አስፈጻሚዉ አካል የኢ-ህገ-መንግስታዊ ጉዳይን በሌላ -ህገመንግስታዊ ዉሳኔ ማስፈጸሙ፤ የክልል ምክር ቤቶች በራሳቸዉ ጉዳይ ባይተዋር መደረጋቸዉ፤ ተገቢዉን ዉይይት አለመደረጉ፣ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ አለመሰራቱ፤እና የሚሰጡ ተገቢ ያልሆኑ አመክንዮች የዉሳኔዉን ቅቡልነት ጎድቶታል፡፡

ዋቤ የተደረጉ ምንጮች

1. Beyene, M. (1970), Time and Police: 1941-1971(Amharic Version). Addis Ababa Ethiopia: Artistic.

2. FDRE Constitution Article 51(6) (1995)

3. Human Rights Watch Collective Punishment (2008), War Crimes and Crimes against Humanity in the Ogaden area of Ethiopia's Somali Regional State,

4. Hagmann, T. (2014), Talking Peace in the Ogaden, The search for an end to conflict in the Somali Regional State in Ethiopia, Nairobi: Rift Valley Institute.

5. International Crisis Group (2013)

6. Ahmed Deeq Hussein, Liyu Police: The Savior. Independent analyst based Jig-jiga.

7. Hagmann T. (2020) ‘Fast politics, slow justice: Ethiopia’s Somali region two years after Abdi Iley ́, Conflict Research Programme, London: LSE.

8. Hagmann, T. (2014), See note 4.

9. Ethiopia Peace Observatory: https://epo.acleddata.com/actor-profiles/#1622661233120-27df4ed3-a6f5

10. European Institute of Peace (2021), Special Police in Ethiopia.

11. Ibid

12. Tiruneh Endeshaw (2020), Assessment of the establishment of liyu police in the Ethiopian federation: the case of selected regional liyu police

13. European Institute of Peace (2021), Special Police in Ethiopia.

14. Tiruneh Endeshaw (2020). See note 12

15. Bereket Tsegay Africa Peace and Security, Development Studies from the School of Oriental and African Studies (SOAS), University of London February 22, 2021by

16. Amnesty International Ethiopia: Police unit unlawfully killing people must be stopped May 31, 2018