የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት በአፍሪካ:- የሃያላኑ የፍልሚያ መስክ

Hailemariam Yirga

8/4/2023

መንደርደሪያ

የመሰረተ ልማት ግንባታ የሃያላን ሃገራት የተፅዕኖ አድማስ ማስፋፊያ ወሳኝ ስልታዊ የፉክክር ሜዳ እየሆነ መጥቷል። ይህም የኢኮኖሚ፣ ደህንነት እና የፋይናንስ የተፅዕኖ መሳሪያዎቻቸውን በታቀደና በተቀናጀ መልኩ ጥቅም ላይ በማዋል የሚፈፀም ይሆናል። የተፅዕኖ አድማሳቻውን ማስፋት የሚፈልጉበትን ሃገር ወይም አህጉር ላይ ትኩረት በማድረግ ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች የሚውል ገንዘብ በዝቅተኛ ወለድ ብድር፣ በእርዳታ ወይም በባለቤት ባለድርሻነት በባንክና በፋይናንስ ተቋማታቸው አማካኝነት ደንብና ቅድመ ሁኔታዎችን በማስረፅ እና ቅቡል እንዲሆን በማስቻል ስምምነት ይፈፅማሉ።

አካላዊ እና የዲጅታል መሰረተ ልማት (physical and digital infrastructure) ግንባታ ዋነኛዎቹ የመፎካከሪይ አውድማ ናቸው። አካላዊ መሰረተ ልማት የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ የዓየር መንገድ ማስፋፊያ የኤሌክትሪክ ተርባይን ተከላና መስመር ዝርጋታ፣ የወደብ ልማት፣ የባቡር መንገድ፣ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዝርጋታ ግንባታ ወዘተረፈ ሲሆኑ፤ የዲጅታል መሰረተ ልማት ግንባታዎች ትኩረት የሚያደርጉት ለዲጅታል ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆኑትን የኢንተርኔት ኔትወርክ መሳሪያዎች ተከላና ዝርጋታ (በተለይ 5G) የውሂብ ማዕከላት ግንባታ፣ የዲጅታል መሳሪያዎች አቅርቦት ወዘተ ናቸው። አሁናዊ ዓለም አቀፍ የመሰረተ ልማት ግንባታ ክፍተተና ፍላጎት ለመሸፈን 15 ትሪሊየን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ በዘንድሮ የሙኒክ ዓለም አቀፍ የፀጥታና ደህንነት ኮንፈረንስ እና G7 በይነመንግስታ የልማት ሪፓርት ላይ ቀርቧል። ይህ የመሰረተ ልማት ግንባታ የንግድ እንቅስቃሴን በማሳለጥ የኢኮኖሚ ልማት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ቢሆንም ለሃያላኑ ሃገራት የፀጥታና ደህንነት ጉዳይ እየሆነ መጥቷል።

በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ ሃያላን ሃገራት በተለይም ቻይና፣ አሜሪካና አውሮፓ የተፅዕኖ አድማሳቸውን በአፍሪካ ለማስፉት በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ስለሚደርጉ ፉክክር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደህንነት ስጋት አጋላጭ ስለሚሆንበት እና ለሃገራች ይዞልን ከሚማጣው መልካም አጋጣሚ የአደባባይ የደንህነት መረጃ ምንጮችን (open source intelligence) መሰረት በማድረግ ለመመርመር እና አፍሪካ እና ኢትዮጵያውያን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው እናጥይቃለን።

የሃያላኑ ፉክክር ለምን?

አሜሪካና አውሮፓ ነባሩን ዓለም ዓቀፍ ሥርዓት ለማስቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ በዋናነት ቻይና የራሷን ደንብና ሁኔታዎች በመቅረፅና ተቋማትን በመገንባት ዓለም አቀፍ የተፅዕኖ አድማስ ለማስፋት እየሰሩ ይገኛል። በአከላዊ መሰረተ ልማት ረገድ የወጪ ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁናቴ የሚያቀላጥፍ፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የማይቋረጥ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር እና ፋብሪካ ለመትከልና ለሥራ ምቹ የሆነ ከባቢ ለመፍጠር ያስችላል። ከፓለቲካ ተፅዕኖ አንፃር ግንባታዎቹ በብድር የሚከናወኑ ስለሆነ ምን ጊዜም ቢሆን ተበዳሪው ሃገር የብድር ወጥመድ ውስጥ ገብቶ የአበዳሪውን ፍላጎት እና እሳቤ በሀገራዊም ሆነ በአለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ በአደባባይ እንዲያንፀባርቅ ተፅእኖ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል።

ከወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሃያልነት ቀጥሎ በዚህ ዘመን ዓለምን ለመቆስጣጠር ወሳኝ የተፅዕኖ መሳሪያ የዲጅታል የበላይነት ነው። የዲጅታል መሰረተ ልማት ግንባታ ይህን የበላይነት ለመጎናፀፍ ዋነኛው መንገድ ነው። ቴክኖሎጅን እራስ ካልፈጠርከው የደህንነት ስጋት ተጋላጭነት ይፈጥራል ይላሉ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች። የዲጅታል መሳሪያዎቹ የተተከሉበትና የተዘረጉበት ሃገር የዜጎችና የተቋማትን ውሂብ (Data) ለመሰብሰብ በቀላሉ ያስችላቸዋል። የውሂብ ሉዓላዊነትን ያሳጣል። የተደበሰበውን መረጃ በማንገዋለልና በመተንተን (Data mining ይሉታል) ለንግድ፣ ለምርምር፣ ለመከላከያ እና ለሌሎች አወንታዊና አሉታዊ ተግባር ማዋል ይቻላል።

በሌላ መልኩ ይህ የውሂብ ሃይል የአንድን ሃገር አመለካከት፣ እምነት፣ ባህሪና ግብር እንደፈለጉ ለመዘወር ያስችላል። ለምሳሌ ቲክቶክ የቻይና ሲሆን ስልተ ቀመሩን እንደፈለጉ በማድረግ በአንድ ሃገር የግጭትና ከፋፋይ መልዕክቶችን በመገደብ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ማድረግ የሚያስችል ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ እነዚህን መልዕክቶች በማናኘት የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት ሃገር የሚፈርስበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይችላል። ከሃራችን አንፃር ካየነው፣ የቻይናዎቹ ህዋዌና ዜድቲኢ የቴልኮም መሰረተ ልማትን የገነቡትና የዘረጉት የራሳቸውን የዲጅታል መሳሪያዎች ሲሆን አብዘሃኛው ህዝብም ቻይና የተሰሩ የእጅ ሰልክና የኢንተርኔት መቀበያ መሳሪያዎችን ይጠቀማል። ይህ የደህንነት የስጋት አጋላጭነት እንደሚፈጥር እሙን ነው። በመሆኑም የዲጅታል መሰረተ ልማት ግንባታ ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሙ ባለፈ የሃገራት የደህንነት ስጋት አጋላጭነት ምንጭ የመሆን አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ልብ ይላሏል።

አሜሪካና አውሮፓ የነባሩን ሥርዓት ከማስጠበቅና አጠናክሮ ከመሄድ አንፃር እና የሃገራት የፀጥታና ደህንነት መሰረታዊ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ በመምጣቱ በተለይም በሙኒኩ የፀጥታ ኮንፈረንስ እንደ ድክመት የተነሳው ተወዳዳሪ የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፋይናንስ አቅርቦት አለመኖር ነው። ይህን ክፍተት ለመሸፈን ባለብዙሃን ተቋማት ጥረት ሲያደጉ አይታይም፣ በተለይ የአለም ባንክ እና ሌሎች የአውሮፓ የፋይናስ ተቋማት ለመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች የሚውል ብድር መስጠት ካቆሙ ረዥም ዘመናት አልፎታል። ለዚህም ነው፣ ለአባይ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ የሚውል ብድር እና እርዳታ ከዓለም ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ልናገኝ ያልቻልነው። ቻይና ይህን ክፍተት በመጠቀም Belt and Road Initiative መርሃግብር በመቅረፅና አንድ ትሪሊየን ዶላር በመበጀት ባለፉት አስር አመታት ከፍተኛ የግንባታ ስራዎችን ባደጉና በታዳጊ ሃገሮች በመፈፀም ነባሩን ስርዓት የሚገዳደር ተፅዕኖዋን ለማስፋፋት አስችሏታል።

ቻይና ምን አተረፈች?

ከላይ በጥቅሉ ለመግለፅ እንደተሞከረው ቻይና ይህን መርሃ ግብር ተግባር ላይ በማዋሏ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖዋን ለማሳደር፣ ከራሷ ኢኮኖሚ እና የንግድ ደህንነት አንፃር የሚከትሉትን ጥቅም አስገኝቶላታል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ከማሳደግ አኴያ ኢንዱስትሪዎቿ በገፍ ያመረቱትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እና እንዲሁም መሰረታዊ የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃዎችን (ማዕድናት) እና ምግብ ለማስገባት አስችሏታል። ከንግድ እንቅስቃሴ ደህንነትና ፀጥታ አንፃር ቻይና 80 በመቶ በላይ የሚሆነው ኢነርጂ አቅርቦት በመርከብ የምታስገባ ሲሆን ከአሜሪካ ጋር ባላት ቅራኔ አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል በየብስ የነዳጅ ማስተላለፊያዎችን በመዘርጋት ስጋት ለመቀነስ ጥረት እያደረገች ነው። ምንም እንኳ ከፍላጎቷ ከፍተኛነት አንፃር ስጋቱን መቅረፍ ባትችልም ዋነኛው የሆነውን የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ንግድ መስመር የሆነውን የማላካ ቀጠናን (Malacca Straint) መሰረተ ልማት እና ደህንነት መዋቅር በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እና መዋለንዋይ በማፍሰስ ላይ ትገኛለች።

መሰረተ ልማትን ታኮ የተፅዕኖ አድማስን በማሳደግ ረገድ ቻይና ተቋማቶቿንና የጥራት ደረጃዎቿን ለማስተዋወቅ፣ ዋነኛ አበዳሪ ሃገር በመሆን ሃገራት የሷ ጥገኛ እንዲሆኑ እና የብድር ወጥመድ (Debt trap) ውስጥ አንቆ ለማስቀረትና በተፅእኖዋ ስር እንዲወድቁ አስችሏታል። የብድር ውጥመድ ውስጥ ከወደቁት መካከል ግብፅ፣ አርጀንቲና፣ ፓኪስታን ዋነኞቹ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የአስተዳደር ዘየዋን ለማስተዋወቅ ረድቷል። መንግስት መር ኢንቨስትመንት እና ብድሩ የአየር ንብረት፣ የማህበራዊ እና የሰብዓዊ መብት መከብርን እንደ ቅድመ ሁኔታ ስለማያስቀምጥ አምባገነን መንግስታትን ይበልጥ የሚያጠናክርና ሙስናን የሚያስፋፋ ሆኑዋል። በዚህም መሰረት በብዝሃ ሃያልን ሃገራት የምትመራ አለም (multipolar world) በመመስረት የቻይናን ጥቅም የሚያስከብር የንግድ ህግጋትን በመደንገግ የበላይነትን ለማረጋጥ እየተንደረደሩ ይገኛሉ።

የአሜሪካና አውሮፓ አማራጭ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አውሮፓና አሜሪካ የቻይናን የማያባራ የጂኦፓለቲካ ፍላጎት ለመከላከል የራሳቸውን አማራጭ ዓለም አቀፍ የመሰረተ ልማት ግንባታ በገንዘብ ለመደገፍ ተነሳሽነት ማሳየት ጀምረዋል። አውሮፓንና የኤዥያን የንግድ ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጅ 2018 በመቅረፅ ስራ ላይ ያዋሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት መርሃ ግብሩ ይበልጥ አለም አቀፍ ተደራሽ እንዲሆን Global Gateway Investment Initiative የተሰኘ 300 ቢሊየን ዩሮ በመበጀት የመሰረ ልማት ግንባታወችን በገንዘብ እየደገፉ ይገኛል። በዚሁ መርሃግብር EU-Africa: global Gateway investment package የተሰኘ 150 ቢሊየን ዩሮ በመበጀት ከህዳር 2022 እኤአ ጀምሮ በአፍሪካ የአረንጓዴ ሃይልና የዲጅታል ሽግግር ለማፋጠን፣ የስራ ፈጠራ፣ የትምህርትና ስልጠና ላይ ትኩረት ባደረጉ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ። የአሜሪካ የባይደን አስተዳደርም እንዲሁ Build Back Better world የተሰኘ መርሃ ግብር በመቅረፅ በየዓመቱ 40 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል። ይህን ተነሳሽነት ይበልጥ ለማጠናከር የጂ-7 ሃገራት የዓለም አቀፍ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ትብብር (PGII) በመመስረት እስከ 2027 ድረስ 600 ቢሊየን ዶላር ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ከዚህ ውስጥ አሜሪካ 300 ቢሊየን ዶላር ለማዋጣት ቃል ገብታለች። ሆኖም ግን ይህ ተነሳሽነት ከቻይና በተለየ የመልካም አስተዳደር፣ የስብዓዊ መብት፣ የአየር ንብረትን መሰረት ያደረገ ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሃገራት ባላቸው ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እንድምታ ላይቀበሉት ስለሚችሉ እና ከቻይና ጎራ እሚመጣውን ፉክክር በበላይነት ለመውጣት ቅድመ ሁኔታወችን ማላላት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ለምሳሌ የአሜሪካ መንግስት በአብይ አስተዳደር ላይ የጦር ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መሰረት አድርጎ ጥሎት የነበረውን እገዳ ሊያነሳ ችሏል። አውሮፓዎችም እንዲሁ። እንዲሁም የብድር ክፍያ ቢሮክራሲው እንደ ቻይና የአንድ መስኮት አገልግሎት ስርዓት የማይከተል ውስብስብ በመሆኑ ይህን ችግር ለመፍታት በጊዜ የለንም መንፈስ እየሰሩ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ እንዴት ትጠቀም

የቻይና የመሰረተ ልማት ግንባታ የብድር ስርዓት የመንግስትን ብድር በከፍተኛ ደረጃ ስላናረው እና ከዚህ በፊት የተበደሩ ሃገራት ለመመለስ የማያስችል የኢኮኖሚ ሁኖታ ላይ ስላሚገኙ የውስጥ ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም ስልታዊ ፍክክሩ የሚቀጥል ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካና በቻይና መካከል ያለው አሁናዊ የጂኦፓለቲካ ውጥረት ቻይናዎች የውስጥ አንድነትና ሰላማቸውን ለማረጋገጥ "ቻይና ታምርት-2025" የተሰኘ የኢንዱስትሪ ፓሊሲ ቀርፀው ትኩረት አድርገው የሚሰሩ በመሆኑ ከፍተኛ ለሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚውል ገንዘብ ያቀርባሉ ተብሎ አይታመንም። ሆኖም ግን የአሜሪካ የባህር ሃይል የበላይነት አንፃር በመርከብ የሚያጓጉዙትን ነዳጅ የስጋት ተጋላጭነት ለመቀነስ ቅድሚያ ከሚሰጡዋቸው መሰረተ ልማቶች መካከል በየብስ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ተከላ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ሃገራችን የአፍሪካ መግቢያ በር፣ በቀይ ባህር ረዥሙን የባህር ጠረፍ የምትሸፍን መሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም የማስከበር ልምድ ያላት መሆኑ፣ እና በዋናነት በቀንዱ ካላት ከፍተኛ የሸማች እና ሰራተኛ የህዝብ ብዛት አንፃር የመሰረተ ልማት ግንባታ ብድር ከቻይና ልናገኝ የምንችልበት እድል ቢኖርም ቻይና ቅድሚያ ከምትሰጠው አንፃር ሲታይ ብዙ ተስፋ ሰጭ አይደለም።

አሜሪካ እና አውሮፓ የሰብሰሃራ አፍሪካ በፍጥነት እየጨመረ የሚሄደው የሕዝብ ብዛት የኢኮኖሚ አቅም ወደፊት ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን በመረዳት እንዲሁም ለኤሌክትሪክ መኪናዎች ባትሪ የሚውል የዓለምን ከሰላሳ በመቶ በላይ የሚሆነው ማዕድን መገኛ በመሆኑ የንግድ እና የጂኦፓለቲካ ተፅዕኗቸውን ከቻይና በበለጠ ለማስፋት የመሰረተ ልማት ግንባታን እንደ አንድ የተፅዕኖ መሳሪያ በመቁጠር ከፍተኛ በጀት መድበው እየሰሩ ይገኛል፡፡ ሃገረችንም ሰብሰሃራ ውስጥ የምትገኝ እንደመሆኑዋ የዚህ ኢንቨስትመንት ተቋዳሽ መሆን ትችላለች፡፡ በተለይም የአውሮፓ ሕብረቱ የመሰረተ ልማት ፓኬጅ ወደ አረንጓዴ ንፁህ የሃይል ምንጭ እና ዲጅታል ቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ስለሆነ ሃገራችን የውሃ፣ የንፋስ እና የእንፋሎት የኤሌክትሪክ ሃይል ምንጭ የሚሆን የተመቸ የተፈጥሮ ሃብት ስላላት ይህን በጀት ለመጠቀም ያስችላታል፡፡ በመሆኑም፣ ይህን ገንዘብ ለመጠቀም የሃገራችን መንግስት በታቀደና በቀናጀ መልኩ በአውሮፓና አሜሪካ እርምጃ ማጥናት፣ መተንተን፣ አማራጭ የጋራ ልማት ፕሮጀክቶች መንድፍ፣ የኢኮኖሚ እና ፖሊቲካል ዲፕሎማሲውን ማጠናከር ያስፈልገዋል። ይህን ከዳር ለማድረስ ደጅ ጠኝ ድርጅት (lobbying firm) ማደራጀት እና መስራት ይገባዋል፡፡ የሚገርመው ነገር፣ ይህን በተመለከተ የአውሮፓ የሎቢ ዳታቤዝ ውስጥ ሃገራችን የቀጠረችው አንድም ደጅ ጠኝ ድርጅት የሌለ ሲሆን ግብፃውያን በተቃራኒው በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚገነቡ ፕሮጅክቶችን የሚቃወም ደጅ ጠኝ ድርጅቶች ቀጥረው በሰፊው እያሰሩ ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ፣ አፍሪካ ካላት የእድገት አቅም አንፃር የሃያላኑ ሃገራት መራኮቻ የተፅዕኖ ማዕከል ሆናለች፡፡ ተፅዕኗቸውን ለማሰረፍ በዋናነት መሰረተ ልማት ግንባታ በማከናወን ፍላጎታቸውን ለማሳካት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ቻይና በተለይ ባለፉት ሃያ አመታት ከፍተኛ መዋለንዋይ በማፍሰስ የተለያየ ግንባታዎችን በመፈፀም ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ልዩ ግንኙነት መስርታለች፡፡ ይህን የተፅዕኖ መፍጠሪያ መሳሪያ አሜሪካና አውሮፓ ቸል ብለውት ቢቆይም ለንግድና ለደህንነት ሲሉ እነሱም ከፍተኛ ገንዘብ በመበጀት የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ለማዋል እየሰሩ ይገኛል፡፡ ሃገራችንም የትኩረት ማዕከላቸው በመሆኑዋ የሃገራችን መንግስት የጂኦፓለቲካ ለውጦችን በመገምገም ለመሰረተ ልማት የሚውል ገንዘብ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻት አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር የአውሮፓውያንና የአሜሪካ ለፕሮጀክት የሚውል ገንዘብ የሚለቁበት የቢሮክራሲ ስርዓት ከቻይናውያን ይለያል። ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት እሳቤያችንን እና እርምጃችንን ከልሶ ማጤን እና ያሉንን ምቹ አጋጣሚዎች በመጠቀም ከሀገራዊ ጥቅም ጋር አስተሳስረን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ከምንም በላይ እነዚህ የኢኮኖሚ ውድድር እና ቀጠናዊ የሃይል የበላይነት ፉክክር ውስጥ አፍሪካ ሀገራት ብሄራዊ ጥቅማቸውን በዘላቂነት እሚያስከብሩበትን እና ተፅእኖ መቋቋም እሚችሉበትን መንገድ በጥልቀት መተለም ይገባቸዋል።

Hailemariam Yirga

Hailemariam has legal and policy science educational background. With considerable experience as a public prosecutor, lawyer, and legal drafter in both the SNNP and Sidama Regions, he has honed his legal expertise. His research focus lies in the intricate domains of the Ethiopian political economy and foreign relations. If you wish to get in touch with him, you may do so via hihoney3@gmail.com