ከገጠር ይዞታ ወደ ከተማ ሊዝ መቀየር፡- በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙርያ ወረዳ ሻራ ቀበሌ ግጭት እና የመሬት ፖሊሲ እንድምታ

ይድነቃቸው አየለ (ዶክተር)

9/14/2023

የግጭት መነሻ

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የከተማ ፕላን 2002 . የተከለሰ ሲሆን፤ በዚህም ክለሳ መሰረት በከተማው ዙሪያ ያሉ ከሰባት ያላነሱ የገጠር ቀበሊያት በከተማ አስተዳደር ውስጥ እንዲካተቱ ይወስናል። ነገርግን ይህ ውሳኔ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይተገበሩ ይቆያሉ:: ከ2012 ጀምሮ እነዚህን ቀበሌያት ወደ ከተማ መስተዳድሩ ለማካተት እንቅስቃሴ የተጀመረ ቢሆንም፤ በሻራ ጫኖ ቀበሌ አስተዳደር ስር ያሉ ገበሬዎች በከተማ አስተዳደር ውስጥ ለመካተት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ይቀራሉ።

ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ይህን የመንግስት ውሳኔ ለማስተግበር በተደጋጋሚ የከተማ አስተዳደሩ እና የቀበሌው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ቢደረግም፤ በአብዛኛው በሙዝ እርሻ ላይ ተሰማርቶ ኑሮውን መሰረት ያደረገው አርሶ አደር ማህበረሰብ ውሳኔውን ለመቀበል እና በከተማ ዉስጥ ለመካተት ፍቃደኛ ሳይሆን ይቃራል። በዋናነት አርሶ አደሩ ማህበረሰብ የገጠር መሬት ይዞታው በከተማ ሊዝ አዋጅ ስር መካታት የይዞታ ደህንነት (tenure security) አደጋ ውስጥ እሚያስገባው በመሆኑ እና ይህም የኑሮ መሰረታቸው (source of livelihood) የሆነውን የሙዝ እርሻ እሚያሳጣቸው በመሆኑ ውሳኔውን ለመቃወም ይገደዳሉ። በሁለተኛነት የመሬቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከከተማ ይዞታ ይልቅ በሙዝ እርሻ የተሻለ ገቢ ሊፈጥር እሚችል በመሆኑ ወደ ከተማ አስተዳደር መካተታቸውን ለመቀበል ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ። በተቃራኒው የከተማ መስተዳደሩ ይህ ችግር ሊከሰት እንደማይችል፣ በከተማ ግብርና ስር green card ሊሰጣቸው እንደሚችል እንዲሁም የሙዝ ምርቱም ለከተማ መስተዳድር ገቢ እሚፈጥር መሆኑን ለማስረዳት ጥረት እንዳደረገ ያስረዳል። ስለዚህም ጉዳይ በተደጋጋሚ ነዋሪውን አወያይቻለሁ ብሎ የዞኑም ሆነ የከተማ መስተዳድሩ ምላሽ የሰጠ ሲሆን በነበራቸው ተከታታይ ውይይት አርሶ አደሩ ዋስትና ማግኘት እና ውሳኔውን ለመቀበል እንዳልቻለ ግን መስተዳድሩ አልሸሸገም::

ግጭት

በዚህ አለመግባባት እና ስምምነት ማጣት ምክንያት ሻራ ጫኖ ቀበሌ አስተዳደር ላለፉተ ከስድስት ወራት በላይ ከከተማ አስተዳደሩም ሆነ ከወረዳው ጋር ያለዉ ግንኙነት የተቋረጠ ነበር። ይህንኑ ተከትሎ የዞኑ አስተዳደር በሰጠው መግለጫ መሰረት ይህ የገጠር ቀበሌ "ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ የታጠቁና ድብቅ ዓላማን ያነገቡ አካላት" ቁጥጥር ስር ያለ በመሆኑ እና "ህገመንግስታዊ ስርዓቱን" ለማስከበር ሲባል እርምጃ መውሰዱን ገልፃል። በዚህም እርምጃ ሰባት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ሲያረጋግጥ የVOA ዘገባ የሟቾች ቁጥር እስከ 18 ሰዎች ሊደርስ እንደሚችል ምስክሮችን ጠቅሶ ዘግቧል። የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ ባደረገው ዳሰሳ እና መጠይቅ መሰረት ከቀበሌው አብዛኛው ወጣት እና ጎልማሳ ወንዶች (አስተዳደሩ የታጠቁ ኃይል እሚላቸው) ለመሸሽ እና ለመደብቅ የተገደዱ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በቀበሌው አብዛኛው ሴቶች እና ህፃናት እንደሚገኙ ይነገራል። በግለሰብ ደረጃ የተገኙ ጥቆማዎች እንደሚያስረዱት አብዛኛው በቀበሌው እሚኖሩ ገበሬዎች በትንሹ ከግማሽ ሄክተር በላይ የሙዝ እርሻ ያላቸው ሲሆን፤ በዚህም የኢኮኖሚ አቅም እና ሐይል ያደረጁ በመሆኑ በከተማ መስተዳድር ዉስጥ መካተታቸውን አጠንክረው ለመቃወም፣ የቀበሌውን ሚሊሻ ለማደራጀት እና ለመከላከል ሙከራ እንዳደረጉ ነው። ነገር ግን በክልሉ ልዩ ሀይል ተወሰደ የተባለው እርምጃ (ምንም እንኳን የክልሉ ልዩ ሃይል መፍረሱ ቢነገርም) ጠንካራ እና ተመጣጣኝ ያልሆነ በመሆኑ ከበድ ያለ ጉዳት በገጠር ቀበሌው ማህበረሰብ ሊደርስበት እንደቻለ ይናገራሉ።

የግጭቱ ስለ ኢትዮጵያ የመሬት አስተዳደር እና ትግበራ እሚያስረዳን እንድምታ

ይህ ግጭት እና ያስከተለው የሰው ህይወት መቀጠፍ እና ንብረት መውደም የገጠር እና ከተማ ልማት እና መሬት ፖሊሲ እና ተግባራቶቻችንን መልሰን እንድንጠይቅ እና የሚከተሉትን አበይት ጥያቄዎች እንድናነሳ ያያደርገናል። በግብርና ህይወት ላይ የተሰማሩት የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ወደ ከተማ መስተዳድር መካተትን ለምን አጥብቀው ሊቃወሙ ቻሉ? የገጠር አካባቢዎች ወደ ከተማ መስተዳድር መካታት ለመሰረት ልማት (ማለትም መንገድ፣ መብራት፣ ጤና፣ ትራንስፖርት፣ የመንግስት አገልግሎት … ወዘተ) ተደራሽ እንደሚያደርግ እና የኑሮ መሰረትን ሊያሻሻል እንደሚችል ሰፋ ያሉ ተርክቶች እና ግንዛቤዎች ቢኖሩም ለምን ማህበረሰቡ የገጠር ይዞታ ስር መተዳድርን እመርጣለሁ ሲል ወሰነ? በእውኑ መንግስት በግድ ወደከተማ አስተዳደር ትካታታላችሁ እሜል ውሳኔ ከመድረሱ በፊት ከማህበረሰብ ጋር መወያያት እና የጋራ መግባባት በገጠሩም ሆነ ከተማ መስፈረት እና ልማት ላይ ስምምነት ወይም ተግባቦት መፍጠር ከበደው? ይህ ግጭት ሀገራዊ የገጠር ልማት እና መሬት አስተዳደር ፖሊሲያችንን ገፅታ እና ክፍትት በምን መልኩ ይገልፃል?

አቻሜለህ ጋሹ ባደረገው ምርምር በከተማ ዙሪያ የመሬት ይዞታ ስርዓት የከተሞች መስፋፋት ተግዳሮቶች እና በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ለውጦች ላይ የተደረጉ ጥናቶች ውስን መሆናቸው ያጠይቃል። በተቃራኒው አንዳንድ ሪፖርቶች እና የምርምር ውጤቶች የከተማ መስፋፋት፣ የገጠር ቀበሊያትን ወደ ከተማ ነዋሪነት መቀየር እና በከተማ ሊዝ ይዞታ ስር የገጠር ይዞታን መካተት የገጠሩን ነዋሪ ይዞታ መብት (tenure security) ለአደጋ እንዳጋለጡት ያትታሉ (ከዚህ ጋር በተያያዘ ዮናስ ተሰማሳሙኤል ገብረስላሴእሸታየሁ እና ሎጋን ያጠኑትን የጥናት ውጤቶች ጋር ማገናዘብ ይቻላል)። የከተሞች መስፋፋት ሁኔታዎች እና የከተሞች መሬት ላይ ፍላጎት ያላቸው አካላት በየጊዜው ተለዋዋጭ እና ውስብስብ ቢሆኑም፤ በጋሞ ዞን አርባምጭ ዙርያ ወረዳ ሻራ ቀበሌ ላይ የተከሰተው ጉዳይ ገበሬው የኑሮ መሰረት ከሆነው ግብርና (source of livelihood) እሚያፈናቅለው እና ለተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጋላጭነት ሊዳርገው እንደሚችል ማህበረሰቡ ስጋት እንደገባው ግልፅ ነው። ከስጋት ባለፈ መልኩ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የከተሞች መስፍፍት ገበሬውን መፈናቀል እና ለተለያዩ ማህበራዊ፣ እኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጋላጭነት ሲገጥማቸው አስተውለናል። ለምሳሌ ያህል በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ገበሬዎች ያጋጠማቸው መፈናቀል ከዚህ ጉዳይ ጋር ተዛማጅ የሆነ ሲሆን ይህንን ተከትሎ የተከወኑ የምርምር ወረቀቶች እነኚህን ችግሮች አጉልተዉ ያሳያሉ (ከዚህ ጋር በተያያዘ አሰበ እና ጓደኞቹ እሚያቀርቡትን ማስረጃ ማየት ይቻላል)። በተቃራኒው የከተማ መስፋፋት ለገጠሩ ማህበረሰብ መሬትን በህገ ወጥ መንገድ በማስተላለፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለገጠሩ ማህበረሰብ የፈጠረ መሆኑ ቢነገርም፤ በተቃራኒው ይህ ህገወጥ ስርዓት ለመሬት ደላሎች እና ተለጣፊ የመንግሥት ሹመኞች የጥቅም ምንጭ እንደሆነ እና ህገወጥ የመሬት ምዝበራ እንዲንስራፉ አመቻችቷል። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናልአዲስወርቅ ጥላሁን እና ሎጋን ኮክራኔ ጃኔ ፕላመር … ወዘተ ባሳተሙት ምርምር ተመሳሳይ ውስብስብ ችግሮችን እና የስርዓት መፋለስ ስር የሰደደ ችግር እንደሆነ ያስረዳሉ።

የአርባ ምንጩ ጉዳይ ልዩ እሚያደርገው የገጠር መሬት ይዞታው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው (land economic evaluation) የእይታን አጉልቶ እሚያሳይ እና አስተማሪ ጉዳይ መሆኑ ነው። በሙዝ እርሻ ተሰማርተው ኑሯቸውን እሚገፉት ገበሬዎች ተቃውሞ የበረታው መሬቱ ከከተማ ይዞታነት ይልቅ በገጠር መሬት ይዞታ ስር የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው ስላመኑ ነው። ገበሬው መሬቱን መስኖ በመጠቅም የሙዝ እርሻ በማልማት በዓመት ውስጥ በአማካኝ ከ3 ጊዜ ባላነሰ ማምረት እና ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ምርታማ እና ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ስለተረዱ መሬቱን ወደ ከተማ አስተዳደር አካሎ ለከተማ ነዋሪ መኖሪያ እና ማህበራዊ አገልግሎት መቀየሩን አልመረጡም። ከዚህ ይልቅ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ እና የኑሮ መሰረታቸውን ላለማጣት ሲሉ ወደ ከተማ ይዞታ ስር መካተቱን ለመቃወም ተገደዋል:: ይህም አሚያስረዳን ገበሬው በዘላቂነት ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሰረቱን እሚያስጠብቅለትን አመዛዝኖ እንደሚረዳ፤ እና ያመነበትን እና የመረጠውን ለማስቀጠል በፅኑ እንደሚታገል ነው።

የከተሞች መስፋፋት እና በዙሪያው እሚገኙ ማህበረሰቦችን የመዋጥ ሂደት የከተሞች ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ይህን ተፈጥሯዊ ሂደት ጤናማ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ልማትን ሊያሰፍን እሚችልበትን መንገድ መንግስት አግባብ ባሉት የከተማ መስፋፋት፣ የገጠር እና ከተማ መሬት ልማት ፖሊሲ እና እሳቤዎችን መንደፍ እና መተግበር ይገባዋል። በተቃራኒው የሀገሪቱ የገጠር መሬት ልማት እሳቤ እና ተግባር ይህን ጉዳይ መሰል ተለዋዋጭ እና ውስብስብ ኩነቶችን ለመገንዘብ እና ለማስተናገድ ግልፅ እና ወጥነት ይጎድለዋል። ሲቀጥል የመንግስት የልማት እሳቤ እና ተግባር ይህንን ከግንዛቤ በመውስድ የገጠሩ ማህበረሰብ በራሱ የኑሮ መሰረት የመወሰን መብቱን ያማከለ እንዲሆን እሚያስችል አይደለም። ከምንም በላይ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲያችንን በአግባቡ የማጥናት፣ የመከለስ፣ ከህዝብ የኑሮ መሰረት (source of livelihood) ጋር እንዲጣጣም፣ የኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እና ዘላቂነት ጋር እሚገናዝብ አይደለም። ይህም በመሆኑ ሀገሪቱ ወጥ የሆነ የመሬት ፖሊሲ ባለመኖሩ ምክንያት እዚህም እዚያም የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ፣ መንግሥት አጠቃላይ የመሬት ፖሊሲ እንዲያወጣ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲወተውቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ይስተዋላል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የከተሞች መስፋፋት እና የገጠር ይዞታዎች ወደ ከተማ ይዞታ እሚቀየሩበትን ስርዓት እና መርህ መርምሮ ግልፅ ስርዓት ማስቀመጥ ያስፈልጋል። በተጨማሪም የመሬቶችን ማህበራዊ እና እኢኮኖሚያዊ ፋይዳን (socioeconomic land evaluation) ከማህበረሰብ ፍላጎት እና የጋራ ልማት አንፃር ማጣጣም እሚቻልበትን መንገዶች ከልሶ ማየት ማደርጀት አስፈላጊ መሆኑን ከላይ የተመለከትነው የአርባምንጩ ጉዳይ አበርክቶ ያስረዳል። ከምንም በላይ ልማት አፈፃፀም ስርዓታችን እኔ አውቅልሀለሁ ወይም አዘምንሃለሁ ከሚል እሳቤዎቻችን ነፃ በሆነ መልኩ የህዝብን ጥያቄ እና ፍላጎት በአግባቡ ማስተናገድ እና የልማት አቅጣጫዎችትንን በጋራ ስምምነት መከወን ይገባናል።

መደምደሚያ

ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የከተሞች በጣም በፍጥነት በማደግ ላይ ናቸው። በዚህም ለመኖሪያ፣ ማህበራዊ እና እኮኖሚያዊ አገልግሎት ግብዓት ይሆን ዘንድ ከፍተኛ የመሬት ፍላጎት ተፈጥሯል። ይህም በከተሞች ዳር ያለው የገበሬዎች ይዞታ የከተሞች መስፋፊያ መስክ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ሽግግር የከተማ ዳርቻዎች ላይ በርካታ ለውጦችን አድርጓል፣ የአከባቢውን ማህበረሰቦች መዋጥ እና የመሬት መብቶችን እና ከግብርና ወደ የተገነባ የንብረት ባለቤትነት መብት ስርዓት መለወጥን እንዲፈጠር አስችሏል። ከዚህም የተነሳ በከተማ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች የተለያየ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መሰረት ባላቸው ሰዎች መካከል ሁሉንም ዓይነት የመሬት ፉክክር እና ግጭት ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል። በዚህ ምክንያት የከተሞች መስፋፋት በከተሞች አካባቢ ነዋሪዎችን የማፈናቀል እና መደበኛ ያልሆነ ሰፈራ እንዲስፋፋ አድርጓል። ስለሆነም የከተሞች መስፋፋት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና በአካባቢው ማህበረሰብ የመሬት መብቶች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቅረፍ እንደ መሬት ማስተካከያ ያሉ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ የሆነ የመሬት ልማት ፖሊሲ እና ትግበራ ማስተዋወቅ ይጠይቃል።

Source: Wekatabti; 2015